Fact checks / Public affairs
False
የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ወደ አሜሪካ ኮበለሉ የሚለው መረጃ የተሳሳተ ነው
ሀቅሰሚ ባደረገው የማጣራት ስራ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የምክክር ኮሚሽኑን ጥለው ኮበለሉ የሚለው መረጃ መሰረት የሌለው መሆኑን አረጋግጧል።
False
ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ሀገር ጥለው አልኮበለሉም፤ ወደ አሜሪካ የሄዱት ለእህታቸው የቀብር ስነ-ስርዓት ሲሆን፣ ተመልሰው ጉባኤውን እየመሩ ይገኛሉ።.

የተሰራጨው መረጃ
የሚጣራው መረጃ
“የምክክር ኮሚሽን ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ከመጨረሻው የውሳኔ ቀን በፊት ወደ አሜሪካ ፈርጥጠው ገብተዋል”
በZene Manchester፣ Ethio Politics Unity እና Anchor Media የፌስቡክ ገጾች ላይ፣ ነሀሴ [day] 2018 ዓ.ም የተጋራ
ሀቅሰሚ ከሰሞኑ ከሀገራዊ ምክክሩ ጋር በተያያዘ በነሀሴ [day] 2018 ዓ.ም Zene Manchester በተሰኘ እና ከ7000 በላይ ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ ገፅ እንዲሁም በ Ethio Politics Unity እና Anchor Media በተሰኙ ገጾች “የምክክር ኮሚሽን ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ከመጨረሻው የውሳኔ ቀን በፊት ወደ አሜሪካ ፈርጥጠው ገብተዋል” በማለት የተሰራጩ መረጃዎችን ተመልክቷል። ይህ መረጃ ከተሰራጨ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ መጋራትና እይታ ያገኘ ሲሆን፣ ከ3000 በላይ ላይክ፣ ከ600 በላይ አስተያየቶችን እና ከ160 በላይ መጋራትን በማግኘት በማህበራዊ ሚዲያው ማህበረሰብ ዘንድ ብዥታ ሲፈጥር አስተውለናል።
The evidence
Explain the verification step, what was found and how it affects the claim.

ሀቅሰሚ ባደረገው የማጣራት ስራ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የምክክር ኮሚሽኑን ጥለው ኮበለሉ የሚለው መረጃ መሰረት የሌለው መሆኑን አረጋግጧል።
ለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ፣ ፕሮፌሰሩ ወደ አሜሪካ አቅንተው የነበረው በቤተሰብ ድንገተኛ ሁኔታ (የእህታቸው ህልፈት) ምክንያት እንጂ ሀገር ጥለው ለመኮብለል እንዳልሆነ ከምክክር ኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያረጋግጣል።
በሁለተኛ ደረጃ፣ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በአሁኑ ወቅት ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በጉባኤው የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ በአካል በመገኘት ሂደቱን እየመሩ ይገኛሉ። ፕሮፌሰሩ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ሀሰተኛ መረጃውን አስተባብለዋል፦
“የነበርኩበትን ሁኔታ ተረድታችሁኛል፣ ከሀገር አልሸሸሁም፤ ከሀገሬ መቸም አልሸሸሁም። ከሀገሬም አልኮበለልኩም። እንኳን በዚህ ዕድሜዬ የዛሬ 40 ዓመት ጉልበት በነበረኝ ጊዜ መውጣት በሚቻልበት ጊዜ ወንድሞቼ ውጭ በነበሩበት እና ‘ና’ ባሉኝ ጊዜም ከሀገሬ አልወጣሁም። እና የቀረችኝን ዕድሜ እዚሁ ነው የማሳልፈው”

በሦስተኛ ደረጃ፣ የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ነሐሴ 13 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጡት ይፋዊ መግለጫ፣ ኮሚሽኑ ከ120 በላይ አጠናቃሪ ተሳታፊዎችን በማስተባበር የውይይት ሰነዶችን አጠናቆ ለ4 ሺህ ተሳታፊዎች ለማቅረብ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝና ሂደቱ በተያዘለት ሰሌዳ መሰረት እየተመራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ በበይነ መረብ ላይ ያገኘናቸው መረጃዎች ፕሮፌሰሩ የእህታቸውን ሰብለ ጌታቸውን የቀብር ስነ-ስርዓት ነሀሴ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ለመታደም በአሜሪካ ሜሪላንድ እንደነበሩ የሚያሳዩ መረጃዎችን ማግኘት ተችሏል። በጥሪ መግለጫው ላይም የፕሮፌሰሩ ስም በጽሁፉ ግርጌ ስር ሰፍሮ እናገኘዋለን።

ለምን አስፈላጊ ነው
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ ባሉ መሠረታዊ እና አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ በህዝብና በፖለቲካ ሀይሎች መካከል ሰፊ ውይይት በማድረግ ዘላቂ መግባባት ለመፍጠር በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋም ነው።
የኮሚሽኑ ዋና ዓላማም እንደ ህገ-መንግስት፣ የፌደራሊዝም ቅርፅ፣ የታሪክ ትረካዎች እና የወሰን ጥያቄዎች ባሉ አከራካሪ ርዕሶች ላይ በስፋት በመወያየት የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ ሲሆን፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ልዩነቶችን በኃይል ፈንታ በሰለጠነ የጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር የማስወገድ ባህልን ማዳበር ነው።
ይህንን ዓላማ ለማሳካት ኮሚሽኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ማህበራትን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በወረዳ፣ በዞን፣ በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ አሳታፊ የምክክር መድረኮችን ያዘጋጃል። በዚህ ሂደት የተለዩ አጀንዳዎችን እና የተሰበሰቡ የውሳኔ ሀሳቦችን አጠቃሎ ለህዝብና ለሚመለከታቸው አካላት የሚያቀርብ ይሆናል።
ተቋሙን በዋና ኮሚሽነርነት የሚመሩት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የረጅም አመታት የምርምር ልምድ ያላቸው ታዋቂ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን በኃላፊነት ሲመሩ ቆይተዋል።
ማጠቃለያ
ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ሀገር ጥለው ኮበለሉ በሚል በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው መረጃ የተፈበረከ እና ሀሰተኛ መሆኑን ሀቅሰሚ ማረጋገጥ ችሏል።
Sources
- Zene Manchester፣ የፌስቡክ ፖስት፣ ነሀሴ [day] 2018 ዓ.ም
- Ethio Politics Unity፣ የፌስቡክ ፖስት
- Anchor Media፣ የፌስቡክ ፖስት
- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ የምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ መግለጫ፣ ነሐሴ 13 ቀን 2018 ዓ.ም
- ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ በጉባኤው የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር
- የሰብለ ጌታቸው የቀብር ስነ-ስርዓት የጥሪ መግለጫ፣ ሜሪላንድ
እርማቶች
በዚህ ጽሑፍ ላይ ምንም እርማት አልተደረገም። ስህተት አግኝተዋል? እርማት ይጠይቁ።